የኢትዮጵያ አየር መንገድ – Mesfin Ashagre – Paris

ታሪክን ለማያውቁ

                    ቁጥር 1       የኢትዮጵያ አየር መንገድ።

ዛሬ የሀገራችን የዓመታት ታሪኳና ለዚህም ታሪኳ በተለያየ ወቅትና መድረክ ላይ የተሳተፉ ልጆቿ ሲወቀሱ፣ ሲደነቁ፣ ሲታሙ፣ ሲተቹና ሲሰደቡ መስማትና ማንበብ በበዛበት ሰዓት ላይ ምን ያህል የገዛ አገራችንን ታሪክና የመሪዎቿን ግዙፍ ስራ ብዙ የተረዳንና የምናውቅ ያለን አይመስለኝም። ይህ ሁኔታ ካልታረመና ካልተስተካከለ ትናንትን ያላወቀ ዛሬን ማጣጣም ነገን መቀየስ ይቻለለዋል ብዬ ለመናገር ያዳግተኛልና ለዚህ ዕርማት አንዳንድ የኢትዮያን የኩራት መዋቅሮች እንዴትና በማን እንደታቀዱና ዕውን እንደሆኑ ማስታወሱ ለአሁኑ በሶሻል ሜዲያና በሀሰት ፖለቲካ ለታወረውና ካላግባብ ስምና ታሪካቸውን ከመበከል አንሶ ማስታወሻ ሀውልታቸውን ላፍርስ ላጥፋ ብሎ የተነሳውን ጭፍን ትውልድ ከስህተቱ ያስቆመዋል በሚል ስላመንኩበት ነው።

የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በላዩ ላይ እያውለበለበ የምድር ላይ ጀግንነታችንን በሰማዩም ላይ ከፍ ብሎ እንዲታይ ያደረገንን ትልቁ የጋራ ሀብታችንን የኢትዮጵያን አየር መንገድ አነሳስና አመጣጥ ያለኝን ዕውቀቴን ላካፍላችሁ።

አጼ ሀይለ ሰላሴ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የሚያስኮሩ፣ የሚያስከፉ፣ የሚያናድዱ ሌሎችንም ስሜቶች የሚያሰሙ ብዙ ነገሮችን ሰርተዋል። ከነኝህም አንዱና ዋናው ዛሬ ከአፍሪካ 1ኛ ዓለም ላይ ካሉት የታላላቅ አገሮች የበረራ ድርጅቶች ጋር ደረቱን ነፍቶ መደራደርና መፎካከር የሚችለውን አየር መንገዳችንን የፈጠሩ ንጉስ ናቸው።

የሰማይ በረራ ወይም አህጉር የማቈረጥና ጉጉት ኖሯቸው ብቻ አልነበረም ይህንን ካምፓኒ የፈጠሩት። ምክንያቱ ምን እንደነበረ ታሪኩን ስታውቁት ይበልጥ ትረዱታላችሁ። ንጉሱ ለአፍሪካ ህዝብ በነጻነት አብሮ መኖርና ማደግ የዕለት ዕለት ችግራቸውና የህሊና ጭንቀታቸው መነሻ ርዕሳቸው እንደነበር የአፍሪካን አንድነት ድርጅት May 25/1963 ዓ/ም በትኩሱ ከቅኝ ተገዥነት ነጻ ከወጡ 32 የአፍሪካ አገሮች ፊት አዲስ አበባ ላይ መስራቹን ታሪካዊ ንግግር ማንበቡ ዓይናችንን ብቻ ሳይሆን ህሊናችንንም ከፈት ያደርጋል ብዬ እገምታለሁ። ይህንን ታሪክ በተከታይ ሌላ ጽሁፍ ላይ እመጣበታለሁ።

 

ዛሬ ከ120 በላይ የበረራ መስመሮች ያለውና የኢትዮጵያን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላም በዓለም እና  በራሳችን ላይ ጎላ ብሎ የሚታየውና የዜግነት የኩራታችን ምልክት የሆነው አየር መንገዳችን ዕቅዱ የጀመረው በ1929 እ/አ/አ ነበር። የመጀመሪያውም አውሮፕላን Potez 25 በፈረንሳይ የተሰራው የመጀመሪያ በረራውን አዲስ አበባ አካባቢ ነበር ያደረገው። ይህንንም ታሪካዊ ቀን ዘላለማዊ መታሰቢያ እንዲሆን ተብሎ በንግስት ዘውዲቱና በአጼ ሀይለ ስላሴ ፊት የፖስታ ቴምብር ታተመ።

ይህንንም የመጀመሪያ በረራውን ካደረገ በኋላ ሁልጊዜ በራሱና በማንነቱ የሚኮራው የኢትዮጵያ ህዝብ የራሱን ዜጎች በፓይለትነት ማስተማርና ማሰልጠን ጀመረ። በዚያን ወቅት አገሪቷን ከመሀል ከተማ እስከ ጅቡቲ ድረስ የሚያገናኛት መጓጓዣ የምድር ባቡር ነበር። የመኪና መንገዶች አብዛኛውን ጊዜ በገንብ ባለመሰራታቸው በዝናብና በጎርፍ እየተጥለቀለቁ አስተማማኝ ግልጋሎትን አይሰጡም።

ይሁንና ይህ የሰለጠነና አስተማማኝ ጉዞን በአየር የማድረጉ ዕቅድ መንገድ ላይ ባለበት ሰዓት ላይ ከተጀመረ ገና 6ተኛ ዓመቱ ላይ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ1935 እ/አ/አ በፋሽሽት ጣሊያን ወረራ ምክንያት ተቋረጠ።

ከ5 ዓመታት ትግል በኋላ ነጻነቷን መልሳ ያገኘችው ኢትዮጵያ በአጼ ሀይለ ስላሴ አንሳሽነት የመጀሪያ የጦር ሀይል እቅዷን ዘመናዊ የአየር ሀይል ለማቋቋም ይወስናሉ።

መስከረም ወር 1945  ከአሜሪካው TWA( Trans-World Airlines) ጋር በመተባበር የመጀመሪያው የንግድ በረራ ተጀመረ።በኋላም ድርጅቱ እየተጠናከረ መጥቶ የመጀመሪያ መጠሪያ ስሙ Bring Africa Together !  (የአፍሪካን ህዝብ አሰባሳቢ)  በመባል ዓለም ዓቀፍ በረራውን ጀመረ።

የመጀመሪያው ዓለም ዓቀፍ በረራ የጀመረው April 1946 ሙከራውን ያደረገው ካይሮ ግብጽ ሲሆን የፈጀበትም የበረራ ሰዓት 10 ሰዓት ነበር። ይህ ከሆነ 1 ዓመት በኋላ ወደ ህንድ ቦምቤይ ከተማ በየመን ኤደን ላይ ዕረፍት አድርጎ የሚደርስ በረራ ነበር። የአገር ውስጥ የመጀመሪያ በረራዎች ይካሄዱ የነበረው አስተማማኝ በሆኑ Dakota DC3 ሆኖ ቆይቶ ከ1950 በኋላ የዳበረና ስፋት ያለው ዓለም ዓቀፍ በረራ ለማድረግ ተወሰነ። ለዚህም 26 መንገኞችን የሚይዙ 2 Convair 240s አውሮፕላኖች ስራ ላይ ዋሉ።

የመጀመሪያው የነዚህ አውሮፕላኖች በረራ ከፍተኛ ቦታ ላይ ለሚገኘው አዲስ አበባ አየር መረፊያ ችግሮችን ፈጠረ። ምክንያቱም አውሮፕላኑ የተሞላው ነዳጅኛ የተሳፈሩት መንገደኞች ክብደት ለመብረር የመነሳት አቅሙን አዳከሙት።ይህንንም ችግር ለመፍታት ተብሎ ከባህር ጠለል በታች የምትገኘው ድሬዳዋ ከተማ  ጊዚያዊ መፍትሄ እንድትሆን ተመረጠ። ለዚህም አውሮፕላኑ ከአዲስ አበባ እስከ ድሬደዋ በሚበቃው ነዳጅ ይበርና እዚያም ካረፈ በኋላ ለዓለም ዓቀፍ በረራ የሚያስፈልገውን ሙሉ ነዳጅ ሞልቶ ካለ ዕንቅፋት ክንፉን ዘርግቶ ለመብረር ቻለ።

በኋላም  በ1960 convairs የሚባለው አውሮፕላን በDouglas DC-6Bs አዲስ አበባ ላይ የመጀመሪያ የፓይለቶች ማሰልጠኛ ት/ቤት ተከፍቶ ተማሪዎች ለስልጠና ባህር አቋርጠው መሄዱን ተውት።

ከዚያም በጀት ወቅት ስንገባ የኢትዮጵያም አየር መንገድ ከቦይንግ ፋብሪካ ጋር ወዳጁነቱን አጠናክሮ የመጀሪያውን ቦይንግ 720Bs በመግዛት ስሙን በአጭሩ ETHIOPIAN Airlines በአጭር የኢትዮጵያ ስም ተክቶት በ1984 ላይ 3 የረጅም በረራ ቦይንጎችን በማዘዝ ከዓለም የመጀሪያው በህዝብና በመንግስት ስር ያለ አየር መንገድ ለመሆን በቃ።

በ1980 ዎቹ በፈረንሳይና በጣሊያን የሚሰራውን ለመካከለኛ ጉዞ የሚጠቅሙትን ATR-42s እና ለካርጎ ግላጋሎት የሚጠቀምበትን Lockheed L-100 አውሮፕላኖች ገዛ። በኋላም በ1990 እና 1991 ላይ 4 ሌሎች ቦይንጎችን በመግዛት ግልጋሎቱንና በረራውን እስፋፍቶ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ላይ ደርሷል።

ከ1991 ዓ/ም ጀምሮ የተሰሩ በጎ ነገሮች ቢኖሩም ሌሎችም አሳፋሪና አስቀያሚ ድርጊቶችም በዙሪያው ተድረገዋል። ይህን የመጀመሪያ የታሪክ ዘገባዬን በዚሁ ልቅጨው።

አጼ ሀይለ ስላሴ አገራችንን ብቻ አልነበረም በአንድነነትና በፍቅር አብረን እንኑር ያሉት አፍሪካንና ህዝቦቿንም ጭምር ነበር። ለዚህ ስራቸው እንኳን ክብር እንጅ ጥላቻና ንቀት አይገባቸውም ነበር።

 

                                                           መስፍን አሻግሬ ከፈረንሳይ

ሐምሌ 24/2012

About expeder

Check Also

ከኢትዮጵያዉያን ማህበር በአዉሮፓ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

PressRelease-AMHARIC- by A.E.E-March 23-2024

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

68 + = 73